+251 25 111 2233 info@diredawaedu.gov.et
Back to News
ማስታወቂያ May 14, 2026 Dire Dawa Administration Education Bureau

ለ5ኛ፣ 7ኛ እና 11ኛ ክፍል ተማሪዎች የስታንዳርድ ፈተና ውሳኔ ማስታወቂያ

የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አዲስ ውሳኔ አስታውቋል፡ ለ5ኛ፣ 7ኛ እና 11ኛ ክፍል የሚሰጠው የስታንዳርድ ፈተና እንደ ትምህርት ቤት ፋይናል ፈተና ውጤት ይቆጠራል።

ለ5ኛ፣ 7ኛ እና 11ኛ ክፍል ተማሪዎች የስታንዳርድ ፈተና ውሳኔ ማስታወቂያ

ማስታወቂያ

የ2018 ዓ.ም የ5ኛ፣ 7ኛ እና 11ኛ ክፍል ፈተና በትምህርት ቢሮ የሚዘጋጅውን እስታንዳርድ ፈተና በሁሉም የመንግስት እና የግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት ፋይናል (Final) ፈተና ሆኖ ለተማሪዎች እንዲያዝ ስለማሳወቅ

የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና የተማሪዎችን ትክክለኛ የብቃት ደረጃ ለመመዘን የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቃል።

ከዚህ ቀደም በየዓመቱ ሲሰጥ የነበረው የስታንዳርድ ፈተና ለጥናት እና ለምክረ ሃሳብ ማቅረቢያነት ብቻ ይውል የነበረ ቢሆንም በዚህ ሂደት ውስጥ በተለይም የተማሪዎችን ትክክለኛ የትምህርት ደረጃ ለማወቅ እና በትምህርት ቤቶች በኩል የሚታዩ የምዘና ክፍተቶችን ለመቅረፍ እንዲቻል አዲስ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በመሆኑም በ2018 ዓ.ም በሁሉም የመንግስት እና የግል ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የስታንዳርድ ፈተናን በተመለከተ የሚከተሉት ውሳኔዎች መተላለፋቸውን እናሳውቃለን፡-

  1. ፈተናው የሚሰጥባቸው ክፍሎች፡ የስታንዳርድ ፈተናው ለ5ኛ፣ 7ኛ እና 11ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚሰጥ ይሆናል።
  2. የውጤት አያያዝ፡ ፈተናው በተጠቀሱት የትምህርት አይነቶች ተማሪዎች የሚፈተኑት ሆኖ፤ ውጤቱም ከ40 (አርባ) ነጥብ ተይዞ እንደ ትምህርት ቤቱ የፋይናል (Final) ፈተና ውጤት የሚቆጠር ይሆናል።
  3. የፈተና ዝግጅት፡ ፈተናው በማዕከል በትምህርት ቢሮ የሚዘጋጅ በመሆኑ ትምህርት ቤቶች በእነዚህ የክፍል ደረጃዎች እና የትምህርት አይነቶች የራሳቸውን የፋይናል ፈተና የማያዘጋጁ መሆኑን እናሳውቃለን።
  4. ዝግጅትን በተመለከተ፡ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው ለዚህ በማዕከል ለሚዘጋጀው ፈተና ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እና ክትትል ከወዲሁ እንዲያደርጉ በጥብቅ እናሳስባለን።

የዚህ ለውጥ ዋነኛ ዓላማ የምዘና ስርዓቱን ወጥ፣ ግልጽ እና ጥራቱን የጠበቀ በማድረግ የተማሪዎችን ትክክለኛ የዕውቀት ደረጃ ለማወቅ እንዲቻል በመሆኑ ሁሉም የትምህርት አመራሮች፣ መምህራን እና ባለድርሻ አካላት ለተግባራዊነቱ የበኩላችሁን እንድትወጡ እናሳውቃለን።

የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ

Share: